መርማሪ ፖሊስ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ የአካባቢ ግጭቶች እጃቸው እንዳለበት መርማሪ ፖሊስ አስታወቀ

የብሄራዊ የመረጃና ደህንነት የመምሪያ አዛዥ ናቸው ብሎ መርማሪ ፖሊስ ከሰኔ 16ቱ የቦምብ ፍንዳታን በማስተባበር ተጠርጥረው በምርመራ ላይ የሚገኙት አቶ ተስፋዬ ኡርጌ፤ በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች የሚሰሱ ግጭቶች እጃቸው እንዳለበት መርማሪ ፖሊስ አስታወቀ።

እንደ መርማሪ ፖሊስ ገለፃ፥ ይህንን ተከትሎ በተደረገ ምርመራም ቦምብ እና የጦር መሳሪያ እንደተገኘባቸውም ጠቁሟል።

ሌላም ያልተያዘ የጦር ማሳሪያ እንዳለ የጠቆመው ፖሊስ፤ ይህንን ለመያዝ እየሰራ መሆኑንም ለፌደራሉ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ተረኛ 1ኛ የወንጀል ችሎት አስረድቷል።

እንዲሁም በአዲስ አበባ ከተማ እና ከአዲስ አበባ ከተማ ውጭ ያሉ ተጨማሪ የቃል ምስክሮችን ለመቀበል ተጨማሪ የ14 ቀን ጊዜ ይሰጠኝ ሲል ፍርድ ቤቱን ጠይቋል።

የተጠርጣሪ ጠበቃ በበኩላቸው ተጠርጣሪው እጃቸው ከተያዘ 43 ቀን በመሆኑ በዚህ ጊዜ ውስጥ በተሰጠ ተጨማሪ ጊዜ ፖሊስ ተመሳሳይ ጥያቄ ማንሳቱን ጠቁመዋል።

ጠበቃው አክለውም መጀመሪያ ከተጠረጠሩበት ከሰኔ 16ቱ የቦምብ ፍንዳታ ውጭ አሁን ተጨማሪ ጊዜ እየተጠየቀባቸው ያለው በሌላ ወንጀል ነው፤ ይህ ተገቢ አይደለም ያሉ ሲሆን፥ ይህ የመርማሪ ፖሊስን አሰራርም ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነውም ብለዋል።

ደንበኛዬ በዋስ ሊወጣ ይገባል ሲሉም የመርማሪ ፖሊስን የተጨማሪ ጊዜ ጥያቄ ተቃውመዋል።

ፍርድ ቤቱ በበኩሉ መርማሪ ፖሊስ ተጠርጣሪው አቶ ተስፋዬ ኡርጌ የተጠረጠሩበትን ዋና ጉዳይ እንዲያብራራ የጠየቀ ሲሆን፥ የተጠረጠሩበት የግድያ ነው ወይስ የወንጀል ነው ሲል መርማሪ ፖሊስ ግልፅ እንዲያደርግ ጠይቋል።

መርማሪ ፖሊስ በሰጠው ማብራሪያም አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ከእሳቸው በላይ እና በታች ካሉ ካልተያዙ ገብረአበሮቻቸው ጋር በመሆን የሰኔ 16ቱን የቦምብ ፍንዳታ በማስተባበር እንዲፈነዳ አድርገዋል፤ በዚህም የ2 ሰው ህይወት አልፏል ብሏል።

በተጨማሪም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ግጭቶች እንዲነሱ በማድረግ በሽብር ወንጀል የሚጠረጠሩ እንደሆነ እና በዚህ ላይ መርመራ እያደረገ መሆኑንም አብራርቷል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ በተደረገ ምርመራም ቦምብ እና የጦር መሳሪያ እንደተገኘባቸውም መርማሪ ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

የተጠርጣሪ ጠበቃው በበኩላቸው፥ የመርማሪ ፖሊስ ምክንያት ተመሳሳይ ነው፤ ከሰኔ 16ቱ የቦምብ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ የሌሎች ተጠርጣሪዎች ምርመራ ተጠናቆ ሳለ ለብቻቸው በሌላ ወንጀል ምርመራ በሚል ተጨማሪ ጊዜ ሊጠየቅ አግባም ሲሉ ተቃውሟቸውን አቅርበዋል።

ፖሊስም ከእሳቸው ጋር ተጠርጥረው በምርመራ ላይ የሚገኙ ሌሎች ተጠርጣሪዎች ምርመራ አለመጠናቀቁን እና እስካሁንም ክስ እንዳልተመሰረተ ለፍርድ ቤቱ አስረድቷል።

የግራ ቀኙን ክርክር የተመለከተው ፍርድ ቤቱም አቶ ተስፋዬ ኡርጌ የተጠረጠሩበት የወንጀል ሁኔታ ወደ ሽብር የሚወስድና ክብደት ያለው ነው፤ ይህ ደግሞ ምርመራው በቀናት ብቻ የሚገመት አይደለም ዓመታትንም ሊወስድ ይችላል በሏል።

ፍርድ ቤቱ ከወንጀሉ ክብደት እና ውስብስብነት አንፃርም የዋስትና ጥያቄውን ወደ ጎን በመተው መርማሪ ፖሊስ የጠየቀውን የ14 ቀን ተጨማሪ ሙሉ ጊዜ ሰጥቼዋለሁ ሲል ፈቅዷል።



Source: Fana Broadcasting