ህግ የማስከበርና የማስፈፀም አቅሜ ፍትሃዊነት የጎደለውና ሰፊ ክፍተት ያለበት ነው – የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ

ህግ የማስከበርና የማስፈፀም አቅሙ ፍትሃዊነት የጎደለውና ሰፊ ክፍተት ያለበት መሆኑን በጥናት ማረጋገጡን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል።

የፌዴራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ፀጋዬ በተቋሙ የ2010 እቅድ አፈፃፀምና የ2011 እቅድ ውይይት ላይ እንደገለጹት እነዚህን ችግሮች ከመሰረቱ ለመቀየር መንግስት የተለያዩ መሻሻዎችን እያደረገ ነው።

በዚህም መንግስት በፍትህ ስርዓቱ ላይ መሻሻል ባለባቸው ጉዳዮች ላይ ማሻሻያ አየተወሰደ ሲሆን፥ በርካታ ዜጎች የይቅርታ ተጠቃሚ መሆን፣ የትጥቅ ትግል ማቋረጥ፣ የምህረት አሰጣጥ ስነ ስርዓት አዋጅ ማውጣት ከመሻሻያዎች ውስጥ በምሳሌነት ጠቅሰዋል።

ይሁን እንጅ ከህዝብ አመኔታና እርካታ አንፃር የፍትህ ስርዓቱ ዝቅተኛ አፈፃፀም ደረጃ ላይ መሆኑን ነው የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ አቶ ብርሃኑ ጸጋዬ የገለጹት።

በዚህም ህዝብ በተደገጋሚ የሚማረርበትና የህግ የበላይነት ትርጉም ያጣበት የዴሞክራሲ ስራዓት ግንባታ ሂደቱን ገጽታ ያበላሹ ተግባራት በሃገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጸሙ መቆየታቸውን ነው የገለጹት።

የፍትህ ስርዓቱ ነፃና ገለልተኛ በመሆን የህዝብን የህግና የፍትህ ጉዳዮችን ፍላጎትና ጥያቄዎች በሚመለልስ ደረጃ ያለመሆኑም ነው የተገለጸው።

የህግ አስከባሪ ተቋማትም ለፍትህ ታማኝ፣ ለዜጎች መብት ተቆርቋሪ እንዲሆኑ የህዝብ ፍላጎት ቢሆንም የፍትህ ተቋማቱ ይህን ፍላጎት በሚያሳካ ቁመና ላይ ያለመሆናቸውንም አስረድተዋል።

በዚህም በዜጎች ዴሞከራሲያዊና ሰባዊ መብቶች አያያዝ ላይ ክፍተቶች የተፈጠሩ በመሆኑ ሀገሪቱን ላለመርጋጋት ዳርጎጓት የነበረ መሆኑም ነው የተገለጸው።

እነዚህን ሁኔታዎች ለመቀየር መንግስት ጥናት አካሂዶ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸው ዘርፎች የተለዩ ዚሆን ከዚህም መካከል አንዱ የፍትህ ዘርፍ መሆኑን ነው አቶ ብረሃኑ የተናገሩት።

የ2011 የተቋሙ እቅድም በሃገሪቱ አየታየ ያለውን ለውጥ ቀጣይነት ለማረጋገጥና የህግና የፍትህ ስርዓቱን በማሻሻል የፍትህ ስርዓቱ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ የዜጎቹን ሰባዊና ዴሞክራሲያዊ መብት የሚያስከብርና እንዲሆን ለማድረግ በሚያስችልመልኩ መዘጋጀቱን አስረድተዋል።

በሀገሪቱ አንዳንድ አካባቢዎቸ አሁን የተገኘውን ነፃነት አግባብነት በጎደለው የሚጠቀሙ አካላት መኖራቸው የተመላከተ ሲሆን፥ መንግስት የዜጎችን ህይወት የመጠበቅና የህግ የበላይነትን የማስከበር ሃላፊነትቱን ለመወጣት እንደሚሰራም አስረድተዋል።

የህግ የበላይነትን በማስከበር ሂደት ሌሎች ባለ ድርሻ አካላትና ህዝብ በየደረጃው እንዲሳተፍም ጥሪ ተላልፏል።
ውይይቱ እስከሚቀጥለው ቅዳሜ የሚቀጥል መሆኑም ነው የተመላከተው



Source: Fana Broadcasting